የሮም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ከተ.መ.ድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ጋር በመተባበር በተደረገላቸው ድጋፍ በኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል፣ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አወጋገድና ጥቅም ላይ ማዋል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በጣልያን ሬሚኒ እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 8-11 ቀን 2022 Green Technology International Expo በሚል በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ላይ ተሳትፈዋል::

በኤክስፖ ላይ የተሳተፉ ድርጅቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ተሞክሯቸውን በኤክስፖው ላይ በማቅረብ፣ የተሻለ ልምድ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር ቀርበው እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ፈጠራ ክህሎትን ማሳደግ እንዲሁም በጋራ መስራት በሚያስችል ሁኔታ ላይ ውጤታማ ውይይትም አድርገዋል::
ከተሳታፊ መሀል መካከለኛ ድርጅቶች የሆነውና በዘላቂ እና አየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ስራ ላይ የተሰማራው Soil and More ለእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም አቅም ለመፍጠር ASTER ከሚባል የጣልያን ኩባንያ ጋር አብሮ (Joint Venture) ለመስራት ውል ተፈራርመዋል።
ከኤክስፖው ጎን ለጎን የተ.መ.ድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ከጣልያን መንግስት ጋር በመተባበር ለአካባቢ ተስማሚ በሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ (Clean Tech) ውጤታማ ለሆኑ ጀማሪ ድርጅቶች ባዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም ላይ ከተሸለሙት የአምስት ሀገራት የፈጣራ በለቤቶች ውስጥ አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊት ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ ተሸላሚ ሆናለች።
የፈጠራ ባለቤቷ በኢትዮጵያ በሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ማምረት ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ Happy Pads መስራችና ስራ አስፈፃሚም ናት:: በሽልማቱ ወቅት በሰጠችው ገለፃ ምርቱ ለጤንነት ተስማሚ ከመሆኑም በላይ በከፍተኛ ደረጃ የአካባቢ ብክለትንም ያስቀራል ተብሏል::
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳዳር ደሚቱ ሀምቢሳም የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱ ግሪን ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት ድጋፍ ከሚያደርገው የተ.መ.ድ ኢንዱስትሪ ልማት ጋር የተጀመረውን የትብብር ስራዎችን አጠናክረው እንደሚሰሩ ገልፅዋል::
Twitter
Facebook
Instagram