በጣሊያን በተለያዩ ምክንያቶች በተለይም በትህነግ የጥፋት ቡድን ከቤት ንብረታቸው እንዲሁም ከቀያቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ እንዲሆን ለቀረበው የእናት አገር ጥሪ ገቢ የሚሆን የቴሌቶን ዝግጅት ተካሂዷል። ዝግጅቱን የሮም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ከሮም የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ እና በጣሊያን ዲፌንድ ኢትዮጵያ አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ያዘጋጁት ሲሆን በጣሊያን፣ ማልታና ግሪክ እንዲሁም ሌሎች አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ተሳትፈውበታል።
ቴሌቶኑን በጣሊያን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክብርት ደሚቱ ሐምቢሳ በንግግር የከፈቱ ሲሆን በመክፈቻ ንግግራቸው ዳያስፖራው አገር ስትጣራ ሁሌም አለን በማለት ለሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፤ አሁን አገራችን ለሚደርስባት ጫና የዳያስፖረው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም አሁንም እንደበፊቱ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የእለቱ የክብር እንግዳ ታዋቂው አርቲስት ስለሺ ደምሼ/ጋሽ አበራ/ የማነቃቅያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለአገራችን ምንም አይነት የምንቆጥበው ጉልበትም ሆነ ገንዘብ መኖር አንደሌለበት አሳስበዋል፤ በጋራ ከቆምን የማንሻገረው ችግር እንደማይኖር እና ትልቅነት አንድ ከመሆን ብቻ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዕለቱ አትሌት ፋንቱ ሚልኬሳን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችም ንግግር አድርገዋል። የበይነ መረብ ቴሌቶኑን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን በየአካባቢወያቸው በጋራ እና በተናጠል ሆነው ጨረታዎችን በመሳተፍ እንዲሁም ቀጥታ ድጋፎችን በማድረግ ተሳትፈዋል። በበይነመረብ ቶሌቶኑ ከ73,083 ዩሮ በላይ የገንዘብ ድጋፍ የተሰባሰበ ሲሆን በዝግጅቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን አገራቸው በዘርፈ ብዙ ጫናዎች እያለፈች እንደሆነ በውል እንደሚገነዘቡ በመግለፅ ወደፊትም አገራቸው ለምትፈልገው ድጋፍ መልስ ለመስጠት ከወትሮው በተለየ መልኩ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። ዝግጅቱን ክብርት አምባሳደር ደሚቱ ሐምቤሳ በምስጋና ያጠቃለሉ ሲሆን ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ላደረጉት ድጋፍ እና ለአገራቸው ለሚያሳዩት ቀናነት ምስጋና አቅርበዋል።
10