የቆንስላ ፅ/ቤት መከፈትን ምክንያት በማድረግ ከ150 በላይ የሚሆኑ ከሶስቱ ክልሎችና ከጄኖአ ከተማ የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የጄኖአ ከተማ አስተዳደርና አመራሮች፣ አቅም ያላቸው ትላልቅ ባለሀብቶች፣ Confindustria Assafrica እና BonelliErde ከፍተኛ አመራሮች እና የጄኖአ ወደብ አመራሮችና ተቆጣጣሪዎች በተገኙበት በጄኖአ ከተማ ስለ ኢትዮጵያ አሁናዊ ጉዳዮችና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄደ:: ውይይቱን የመሩት በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ክብርት አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ እና የክብር ቆንስል ሆነው የተሾሙት አቶ ጃንፔሮ ሱቺ ሲሆኑ፣ በመድረኩ የጣሊያን የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አምባሳደር ጂዩሴፔ ሚስትሬታ የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተዋል:: በተካሄደው የፓናል ውይይትና ላይ ተሳታፊዎችና አመራሮች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታና አዲሱ የኢኮኖሚ ሪፎርም እና በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል:: በመድረኩ በኢትዮጵያ በሎጂስቲክና ታዳሽ ኃይል ኢንቨስት እያደረጉ ያሉት ኩባኒያዎች በኢትዮጵያ ስላለው ሰላም አስተማማኝ እና ሰፊ ገበያ ያለ መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል:: የጣሊያን ንግድ ማህበር የሆነው Confindustria Assafrica ተወካዮች ማንኛውንም የኢንቨስትመንትና ንግድ እንቅስቃሴ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለማጠናከር የሚፈለግባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል::