የዓለም የሚሌት 2023 ቀንን ምክንያት በማድረግ በሮም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲና የግብርና ሚኒስቴር ትብብር የጤፍ ምርት እንዲሁም ከጤፍ የሚዘጋጁ የተለያዩ የኢትዮጱያ ምግቦችን የማስተዋወቅ ፕሮግራም በሮም የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO) ዋና መ/ቤት ግቢ ውስጥ ተዘጋጅቷል። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ግብርና ሚኒስቴር እና በሮም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ በጋራ ባዘጋጁት የጤፍ ምርቶችንና ምግቦች ዙሪያ ተቀማጭነታቸውን ሮም ያደረጉ የUN ተቋማት ስታፍ፣ ሮም የሚገኙ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች የEU አባላት እንዲሁም የተመድ ተቋማት ሠራተኞች ዝግጅቱን ታድመዋል፡፡ በጣሊያን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጱያ የዘርፈ ብዙ ባህል፣ ሃይማኖትና ወግ ባለቤት የሆኑ ህዝቦች መኖሪያ መሆኗን በመጥቀስ በኢትዮጱያ ብዙ ተወዳጅ የምግብ ዓይነቶች እንዳሉና አብዛኛው ምግብ ደግሞ ከጤፍ የሚዘጋጀው እንጀራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ጤፍ የኢትዮጱያ ገበሬዎች ለሺህ ዓመታት ሲያመርቱት የቆዩና የኢትዮጱያ ሀገር በቀል የሚሌት ዝርያ መሆኑን እና የአገሪቱ መለያ በመሆኑ አንድ አዝርእት በአንድ አገር Commodity Product በሚለው የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት ፕሮግራም ኢትዮጱያ ጤፍን መርጣ እየሰራችበት እንደሆነ ገልጿል፡፡ የቢሎስ ኬክ ቤት እና ጤፍን ኤክስፖርት በማድረግ የሚታወቀውን ሶርስ ጤፍ ካምፓኒ ምስጋና ተደርጎለታል። በዝግጅቱ ከኢትዮጱያ ምግቦች በተጨማሪ የኢትዮጱያ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንስ፣ ቡናና ሌሎች የባህል መገለጫዎች ለታዳሚዎቹ ቀርቧል፡፡