(ሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም): በጣሊያን ሀገር በቬኒስ ከተማ 60ኛው ዓለም አቀፍ የአርት ኤግዝብሽን በዛሬው እለት ተከፍቷል። በወቅቱም በኢግዚብሽኑ ላይ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ባህላዊና የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ በታዋቂው ኢትዮጵያዊው አርቲስት ተስፋዬ ኡርጌሳ የአርት ስራዎች የቀረቡበትን የኢትዮጵያ ፓቪሎን በጣሊያን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክብርት ደሚቱ ሀምቢሳ ተመርቆ ተከፍቷል። በፓቪሎኑ በክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የመደመር መጽሐፍ ለዝግጅቱ ታዳሚያን በማቅረብ በብልጽግና የመደመር መሰረታዊ እሳቤዎች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያዝ የሚያስችሉ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ስነ-ስርዓት እና ሌሎች የሀገራችንን ባህላዊ እሴቶች የሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች ለታዳሚው ቀርበዋል። የኤግዚብሽኑ የኢትዮጵያ ኮሚሽነር የሆኑት በጣሊያን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክብርት ደሚቱ ሀምቢሳ በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ቱሪዝም በሀገራችን ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተከናወኑ አበረታች ስራዎችን ለታዳሚያኑ አቅርበዋል። ክብርት አምባሳደር አያይዘውም አገራችን በጥበብ ስራዎችና በቱሪዝም ሀብት ያላትን የካበተ አቅም እና ከሌሎች የተለየ የሚያደርጋትን በመግለጽ ታዳሚዎች አገራችንን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኤግዚብሽኑ በዓለም ከሚካሄዱ መሰል ዝግጅቶች መካከል ልዩ ክብደት የሚሰጠውና ለስድስት ወራት የሚቆይ ከመሆኑ አንጻር የአገራችንን የጥበብ ስራዎች፣ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲሁም ባህላዊ እሴቶቻችንን በመድረኩ በሰፊው በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ከፍታ በዓለም ዙሪያ በበቂ ሁኔታ ለማሳየት እድል የፈጠረ ነው።
 
Twitter
Facebook
Instagram