(መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም) በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በጣሊያን፣ በግሪክ፣ በማልታና በሳይፕረስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር “ለሀገራችን ብልፅግና በህብረት ቆመናል” በሚል መርህ ቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት አስመልክቶ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ መድረክ ላይ ተገኝተው ስለህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ገለፃ ያደረጉት የህዳሴ ግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጀነር ክፍሌ ሆሮ፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታትም ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ በግንባታው ዘርፍ ልምድ ያላቸውን ሥራ ተቋራጮች ከመቅጠር ጀምሮ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲመቻች መደረጉንም ተናግረዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ 99 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን፣ ከ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ውስጥ የ10 ነጥብ 65 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት መጠናቀቁን፣ የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱንም የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል። ኢንጀነር ክፍሌ ሆሮ፣ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ 95 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ተናግረው፤ ለዚህም የአመራር ቁርጠኝነት እና የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፣ ግንባታው 191 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መድረሱን እና ቀሪ የግድቡን የግንባታ ሥራዎች ለማጠናቀቅም 50 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጨምረው ተናግረዋል። በጣሊያን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ አምባሳደር የሆኑት ክብርት አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በበኩላቸው ዳያስፖራው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንሰቶ እያደረጉት ላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ የተጀመረው ግንባታ ስራ ከዳር እንዲደርስ አሁንም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። ተሳታፊ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው በተደረገላቸው ገለፃ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረው ቀሪውን የግንባታ ሂደት ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

Twitter
Facebook
Instagram