(ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም):- ክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የጣሊያን የካራቢኔሪ ፓሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በክቡር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑካን ቡድን እ.ኤ.አ ጁላይ 2022 ወደ ጣሊያን ሮም ተጉዞ ከጣሊያን ፖሊስ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ ጋር በደረሱበት ስምምነት መሠረት የጣሊያን የካራቢኔሪ ፓሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጎብኝተዋል፡፡ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሲደርሱ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበው ከዚህ ቀደም በሮም ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች አፈፃፀም እና ተጠናክረው በሚቀጥሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። የጣሊያን የካራቢኔሪ ፓሊስ ምክትል አዛዥ ጀነራል ሪካርዶ ጋለኤታአ በውይይታቸው ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጥበቃን የሚያግዙ የፖሊስ ፓትሮል ጀልባዎችን በድጋፍ ለመስጠትና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ፣ በፖሊስ አመራር፣ በፎረንሲክ ሳይንስ እና በቪ.አይ.ፒ ጥበቃ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም ለመገንባት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ እየተገነባ ላለው የፎረንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩትን በማቴሪያል ለማደራጀት ቃል ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋት የሆኑ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተቀናጀና በትብብር ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
 
Twitter
Facebook
Instagram