(መጋቢት 9 ቀን 2016): ተቀማጭነታቸው በሮምሆኖ በግሪክ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክብርት ደሚቱ ሀምቢሳ ከግሪክ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ክብርት አምባሳደር Alexandra Papadopoulou ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። በወቅቱም ክብርት አምባሳደር ደሚቱ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተለይም የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር የደረሰበትን ደረጃ፣ ብሔራዊ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ እንዲሁም ብሔራዊ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አተገባበር አስመልክቶ ለክብርት ሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ክብርት አምባሳደር ሁለቱ ሀገሮች ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት አውስተው፣ በሀገራቱ መካከል ያለው የተጠናከረ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ለሀገራቱ የረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ግንኙነቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ስልጠና ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት አንስተዋል። ክብርት ምክትል ሚኒስትሯ በበኩላቸው ለተሰጣቸው ገለጻ አመስግነው፣ ግሪክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አክለውም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የበለጠ ተቀራርቦ በመስራት ሀገራቱ በንግድ፣ በኢንቨሰትመንት እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
 
Twitter
Facebook
Instagram